Øበአዲስ አበባ ከተማ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓታት ላይ ለሚታየው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅና አደጋ እንዲሁም የከባቢ አየር ብክለት የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች እንዲሁም የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ማንሳት አገልግሎት እና የውበትና መናፈሻ ቦታዎችን ውሃ የሚያጠጡ ተሽከርካሪዎች አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ የእነዚህን ተሸከርካሪዎ ወደ ከተማዋ መግባት የሚችሉበትንና በከተማው ውስጥ የሚንቀሳቀሱበትን ሰዓት በመወሰን ችግሮቹን መቅረፍ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
Øየተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ በሰዓት መገደቡ ፍሰቱን ከማሳለጡም በተጨማሪ በዚህ መመሪያ እንቅስቃሴያቸው የተወሰነላቸው ተሸከርካሪዎችም አገልግሎታቸውን በተቀላጠፈና ወጪን በሚቀንስ መልኩ ማከናወን እንዲችሉ አዎንታዊ ሚና የሚኖረው በመሆኑ፤
Øበአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጭነት፣ ማሽነሪዎችን እና መሰል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 38/2013 ላይ የሚስተዋሉ ለአፈፃፀም እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ለመቅረፍ መመሪያውን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
•ይህ መመሪያ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ክልል በሚገቡና በከተማ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ከተማዋን አቋርጠው በሚያልፉ ከ1 ቶን ወይም ከ10 ኩንታል በላይ የመጫን አቅም ያላቸው የተለያዩ የፈሳሽና የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች እና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
የሰዓት ገደብ ስለመወሰን
1. ማንኛውም የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ እና የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ከጠዋቱ 1፡00 እስከ 3፡00 ሰዓት እንዲሁም ከሰዓት በኃላ ከቀኑ 10፡30 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ወደ ከተማ ውስጥ መግባትም ሆነ በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ፣ ጭነት መጫንም ሆነ ማራገፍ እንዲሁም በዋና ዋና የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው መንገዶች ላይ መቆም የተከለከለ ነው፡፡
2. በዚህ መመሪያ መሠረት ወደ ከተማ መግባትም ሆነ በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ የተከለከለ የጭነት ተሽከርካሪ ወይም ኮንስትራክሽን ማሽነሪ ወደ ከተማው ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ እያለ የሰዓት ገደቡ ቢደርስበት በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ ከዋና መንገድ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ የአካባቢውን የትራፊክ እንቅስቃሴ በማያውክ መልኩ በመቆም የሰዓት ገደቡ እስኪያልፍ መጠበቅ አለበት፡፡
3. ማንኛውም የጭነት ተሽከርካሪ ወይም የኮንስትራክሽን ማሽነሪ በከተማ ውስጥ በእንቅስቃሴ ላይ እያለ በዚህ መመሪያ የተደነገገው የጊዜ ገደብ ቢደርስበት የአካባቢውን የትራፊክ እንቅስቃሴ በማያውክ መልኩ ከመንገድ በመውጣት መቆም አለበት፡፡
4. በዚህ መመሪያ ከተደነገገው ሰዓት ውጭ እንዲሁም እሁድ እና የበአል ቀናት ማናቸውም የጭነት ተሸከርካሪ ወይም የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ወደ ከተማ ውስጥ መግባትም ሆነ በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ፣ ጭነት መጫን ሆነ ማራገፍ ይችላል፡፡
4. የሰዓት ገደብ የማይመለከታቸው ተሽከርካሪዎች
ሀ. ሰሌዳቸው በሀገር መከላከያ ወይም በፖሊስ የተመዘገበ የሀገር መከላከያ እና ሌሎች የፀጥታ ስራዎችን የሚያከናወኑ ከባድና ቀላል የጭነት ተሽከርካሪዎች፤
ለ. በህግ መሠረት የድንገተኛ አደጋ ተሽከርካሪዎች ተብለው የተለዩ የድንገተኛ አደጋ የሚሰሩ ቀላልና ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች፤
ሐ. ነዳጅ የሚያመላልሱ ቦቴዎች
አስተዳደራዊ ቅጣት
1.በተከለከለ ሰዓት ወደ ከተማ ውስጥ በመግባትና በዋና ዋና መንገዶች ላይ ቆመ ብር 10,000(አስር ሺህ ) ይቀጣል፡፡
2.በዋና ዋና መንገድ ላይ የተንቀሳቀሰም ሆነ የጭነት መጫንና ማውረድ ተግባር የፈፀመ ወይም የኮንስትራክሽን ስራ የሰራ ብር 20000(ሃያ ሺህ)ይቀጣል፡፡
3.በመመሪያው የተደነገገውን ቅጣት በመተላለፍ ከተቀጣ በኃላ ለሁለተኛ ጊዜ ጥፋቱን በመድገም የተገኘ ማንኛውም ሰው ከዚህ በላይ የተገለፀውን ቅጣት በእጥፍ ይከፍላል፡፡
4. በተከለከለው ሰዓት በከተማው ውስጥ ሲንቀሳቃስ በመገኘቱ ቅጣት የተጣለበት አሽከርካሪ ሰዓቱ ሳይደርስ የቅጣት ወረቀቱን ይዞ በተከለከለው ሰዓት እንዲንቀሳቀስ አይፈቀድለትም ይህንኑም የትራፊክ ተቆጣጣሪው ፍሰት በማያሰናክል ቦታ ላይ እንዲቆም በማድረግ ቅጣቱን እንዲከፍል ማድረግ አለበት፡፡
5. በተራቁጥር 4 የተቀመጠውን በመተላለፍ ሲንቀሳቀስ የተገኘ አሽከርካሪ የተቆጣጣሪ ትዕዛዝ ባለመፈፀም በመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 395/2009 መሰረት ተጨማሪ ቅጣት ይጣልበታል፡፡
የቅሬታ አቀራረብ
•በዚህ መመሪያ መሰረት በተወሰደ እርምጃ ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም ሰው ቅሬታውን በጽሁፍ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማቅረብ ይችላል፡፡
የመተባበር ግዴታ
ማንኛውም ሰው ይህ መመሪያ በአግባቡ እንዲፈፀም የመተባበር ግዴታ አለበት
የተሻሩ ህጎች
1.በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጭነት፣ ማሽነሪዎችን እና መሰል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 38/2013 በዚህ መመሪያ ተሽሯል፡፡
2. ከዚህ መመሪያ ጋር የሚቃረን ቢሮው ያወጣው መመሪያ ወይም ሰርኩላር እና ልማዳዊ አሰራር በዚህ መመሪያ በተገለፁት ጉዳዮች ተፈፃሚነት አይኖራቸውም፡፡
10. መመሪያውን ስለማሻሻል
ቢሮው ይህንን መመሪያ አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው በማንኛውም ጊዜ ማሻሻል ይችላል፡፡
መመሪያው ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜ
ይህ መመሪያ ከመስከረም 02 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል፡፡